የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎች 200 ኩንታል ዱቄትና 200 ፍራሽ ድጋፍ አደረገ
(አሶሳ፡ መጋቢት 07/2013 ዓ.ም)
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎች 200 ኩንታል ዱቄትና 200 ፍራሽ ድጋፍ አደረገ፡ ፡ ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ የተላኩ አባቶች ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል። የባሕር ዳር ደሴ ካቶሊክ ሰበካ ጉባኤ ጳጳስ ልሣነ ክርስቶስ ማቴዎስ፣ የጳጳሳት ጉባዔዉ ከአሁን በፊትም ለተፈናቃዮች የመፀዳጃ ቤት ግንባታ ከመሥራት ባለፈ የመጠጥ ውኃ ሲቀርብ እንደነበረ አስታውሰዋል። ዛሬ ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎችም 200 ኩንታል ዱቄትና 200 ፍራሽ ድጋፍ መደረጉን ጳጳስ ልሣነ ክርስቶስ ተናግረዋል፡፡
ጳጳስ ልሣነ ክርስቶስ ተፈናቃዮች አስተማማኝ ሠላም ተፈጥሮላቸው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም ጠይቀዋል። የሰው ልጅ የመደጋገፍ ባሕልን ማዳበር ይጠበቅበታል ብለዋል። ቤተክርስቲያኗ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ እስኪመጣ ድጋፋቸዉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው አምራች የነበረ ክቡር ዜጋ በነፃነት፣ በሠላምና በደስታ ይኖርበት ከነበረው ቀየው ተፈናቅሎ ማየት ልብ ይሰብራል ብለዋል። ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ድጋፏን እንደምታደርግ ገልጸዋል። በጥቅሉ ቤተክርስቲያኗ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ከመተከል ዞን ተፈናቅለው ቻግኒ መጠለያ ለሚገኙ ዜጎች ማድረጓን ጠቅላይ ጸሐፊው ገልጸዋል።
"ሕፃናትን በቀያቸው እንዳያድጉ፣ ልጆች እንዳይማሩ፣ ወጣቶች ወደ ልማት እንዳይገቡ እንዲሁም ሽማግሌዎችና እናቶቻችን እንዲፈናቀሉ ያደረጉ አካላት ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ" ጠቅላይ ጸሐፊው ጥሪ አቅርበዋል። በአማራ ክልል የአደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በቻግኒ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ጀምበሩ ደሴ፣ በቻግኒ ወረዳ 48 ሺህ 696 እንዲሁም በጓንጓ ወረዳ ከ19 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አስተባባሪው በኅብረተሰቡ፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በየወሩ ድጋፍ እያቀረቡ እንደሆነ አስረድተዋል። በቻግኒና ጓንጓ ወረዳዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ለሁለተኛ ዙር ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ተናግረዋል። ከክልሉም ሆነ ከፌዴራል በቂ ድጋፍ ባለመቅረቡ ተፈናቃዮች ለሦስተኛዉ ዙር ማግኘት የነበረባቸው ድጋፍ አንድ ሳምንት ማለፉን ተናግረዋል። ይሁንና ድጋፉ ለተፈናቃዮቹ እንዲቀርብ እየተሠራ ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡