በአዲግራት ሀገረስብከት ኢሮብ ወረዳ በጦርነት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ነፍሳተ ሙታን ልዩ ጸሎተ ፍትሐት ተደረገ በአዲግራት ሀገረስብከት የኢሮብ ወረዳ ተወላጅ የሆኑ እና በአዲስ አበባ የሚኖሩ ካቶሊካውያን ካህናት፣ ገዳማውያን እና ምእመናን ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ውድ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም በጦርነቱ ሕይወታቸውን ላጡ ሁሉ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና ልዩ መሥዋዕተ ቅዳሴ እና ፍትሐተ ጸሎት አድርገዋል።

የመሥዋዕተ ቅዳሴው ገባሬ ሰናይ ካህን ክቡር አባ ባዘዘው ግዛው በኢትዮጵያ የሲታውያን ገዳም የበላይ ዐለቃ ሲሆኑ በመርሃግብሩ ላይ ሀዘንተኛ ቤተሰቦች፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጵእጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የማኔጅመንት አባላት፣ የአዲስ አበባ ከቶሊካዊ ሰበካ ጠቅላይ ጽ/ቤት የማኔጅመንት አባላት ቆሞሳት፣ ካህናት፣ ደናግል አና ምእምናን ተገኝተው የሃዘናቸው ተካፋይ ሆነዋል።

ክቡር ዶ/ር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጽ/ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ክቡር አባ ባዘዘው ግዛው በኢትዮጵያ የሲታውያን ገዳም ዐለቃ እና ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽ የማሕበረ ልዑካን ምክትል ዐለቃ በጋራ ባስተላለፉት መልዕክት በማንኛውም ዓይነት ጦርነት ሁልጊዜ ተጎጂ የሚሆኑት ንጹሐን ዜጎች እና ሀገር መሆኗን ገልጸው ይህንን እጅግ አስከፊ ጊዜ በጸሎት እንድናሳልፍ፣ በእግዚአብሔር ብቻ እንድንጽና እና በክርስትናችን በተሰጠን ጸጋ ሁሉን ለእርሱ ፈቃድ እንድንተው ያስፈልጋል ብለዋል።

በመጨረሻም የመጽናናት አምላክ መጽናናትን እንዲልክላቸው በጸሎት እንዲበረቱ ሀዘንተኞቹን በማሳሰብ እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላም እንዲያወርድልን ሁላችንም መጸልያችንን እንድንቀጥል ብለው ጥሪያቸውን ዐደራ ጭምር አስተላልፈዋል። የሞቱት ነፍሳት በእግዚአብሔር ምሕረት በሰላም ይረፉ።