September 26 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ጢሞቴዎስ 5:9-15
9
ዕድሜዋ ከሥልሳ ዓመት ያነሰ መበለት በመዝገብ ላይ አትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤ 10ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለበጎ ምግባር ሁሉ ራሷን በመስጠት በመልካም ሥራም የተመሰከረላት መሆን አለባት።

11ወጣት መበለቶችን ግን እንዲህ ባለው መዝገብ አትጻፋቸው፤ ምክንያቱም ሥጋዊ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ በገቡት ቃል ላይ በሚያይልበት ጊዜ ለማግባት ይሻሉና። 12በዚህም ፍርድን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ በመጀመሪያ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። 13በተጨማሪም ሥራ መፍታትንና ከቤት ቤት መዞርን ይለምዳሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የማይገባውን እየተናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጒዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ። 14ስለዚህ ባል የሞተባቸው ወጣት ሴቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ጠላትም የሚነቅፍባቸውን ነገር እንዳያገኝ እመክራለሁ። 15በርግጥ ከዚህ በፊት አንዳንዶቹ ሰይጣንን ለመከተል ዘወር ብለዋል።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 3:11-18
11
ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን? 12ወንድሞቼ ሆይ፤ በለስ ወይራን ወይንም በለስን ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም።

ሁለት ዐይነት ጥበብ

13ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ የሆነ ሰው ማን ነው? ሥራውን ከጥበብ በሆነ በመልካም አኗኗር ያሳይ። 14ነገር ግን መራራ ቅንአትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኵራት አይሰማችሁ፤ እውነትንም አትካዱ። 15እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ከምድር ከሥጋና ከአጋንንት ናት። 16ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይገኛሉ።

17ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት። 18የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል።

ወንጌል

ዮሐንስ 19:25-27
25
በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። 26በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤ 27ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት።


Previous
Previous

October 3 2021

Next
Next

September 19 2021