September 18 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

ዕብራውያን 11:32-40
የጌታ እራት

32እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ልበል? ስለ ጌዴዎን፣ ስለ ባርቅ፣ ስለ ሳምሶን፣ ስለ ዮፍታሔ፣ ስለ ዳዊት፣ ስለ ሳሙኤል፣ እንዲሁም ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ የለም። 33እነዚህ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በቅን ፈረዱ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀበሉ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ 34የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀያል ሆኑ፤ ባዕዳን ወታደሮችን አባረሩ። 35ሴቶች ሙታናቸው ተነሡላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የተሻለውን ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ፣ መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም። 36አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ፤ 37በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተወግተው ሞቱ፤ እየተጐሳቈሉ፣ እየተሰደዱና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ቈዳ ለብሰው ዞሩ፤ 38ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውምና። በየበረሓውና በየተራራው፣ በየዋሻውና በየጒድጓዱ ተንከራተቱ። 39እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም ከእነርሱ ማንም የተስፋውን ቃል የተቀበለ የለም። 40እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገር ስላዘጋጀ፣ ያለ እኛ ፍጹማን ሊሆኑ አልቻሉም።

ሁለተኛ ምንባብ

ራእይ 6:9-11
9
አምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ። 10እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ “ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?” አሉ። 11ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው።

ወንጌል

ማቴዎስ 23:23-39
23
“እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ 24እናንት የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ።

25“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ትወለውላላችሁ፤ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ስስት ሞልቶባቸዋል። 26አንተ ዕውር ፈሪሳዊ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል።

27“እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ውጫቸው በኖራ ተለስነው የሚያምሩ፣ ውስጣቸው ግን በሙታን ዐፅምና በብዙ ርኵሰት የተሞላ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ! 28እናንተም በውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በክፋት የተሞላ ነው።

29“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር እየገነባችሁ፣ የጻድቃንንም ሐውልት እያስጌጣችሁ፣ 30‘በአባቶቻችን ዘመን ብንኖር ኖሮ፣ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁና። 31በዚህም የነቢያት ገዳዮች ለነበሩት አባቶቻችሁ ልጆች መሆናችሁን በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። 32እንግዲህ የአባቶቻችሁን ጅምር ተግባር ከፍጻሜ አድርሱ!

33“እናንተ እባቦች፤ የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ልታመልጡ ትችላላችሁ? 34ስለዚህ ነቢያትን፣ ጠቢባንንና መምህራንን እልክላችኋለሁ፤ ከነዚህም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ ሌሎቹንም በምኵራቦቻችሁ ትገርፏቸዋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ታሳድዷቸዋላችሁ። 35ስለዚህ፣ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው ንጹሕ ደም ሁሉ እናንተ ተጠያቂዎች ናችሁ። 36እውነት እላችኋለሁ፤ ላለፈው ነገር ሁሉ ይህ ትውልድ ይጠየቅበታል።

37“አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ አንቺ ኢየሩሳሌም! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን ፈቃደኛ አልሆናችሁም፤ 38እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል! 39እላችኋለሁና፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስከምትሉ ድረስ ዳግመኛ አታዩኝም።”

Previous
Previous

September 25 2022

Next
Next

September 11 2022