October 30 2022
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 7:1-13
የጋብቻ ምሳሌ
1ወንድሞች ሆይ፤ ሕግን ለሚያውቁ ሰዎች እናገራለሁ፤ ሕግ በአንድ ሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው፣ ሰውየው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን አታውቁምን? 2አንዲት ያገባች ሴት ከባሏ ጋር በሕግ የታሰረች የምትሆነው እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ነው፤ ባሏ ቢሞት ግን ከጋብቻ ሕግ ነጻ ትሆናለች። 3ነገር ግን ባሏ በሕይወት እያለ ሌላ ሰው ብታገባ አመንዝራ ትባላለች፤ ባሏ ቢሞት ግን ሌላ ሰው ብታገባም እንኳ፣ ከዚያ ሕግ ነጻ ትሆናለች፤ አመንዝራ አትባልም።
4ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተም በክርስቶስ ኢየሱስ ሥጋ ለሕግ ሞታችኋል፤ ይህም ከሙታን ለተነሣው ለእርሱ፣ ለሌላው ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ ነው። 5ኀጢአተኛ በሆነ ተፈጥሮ ቊጥጥር ሥር ሳለን፣ ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሕግ የተቀሰቀሰው የኀጢአት መሻት በሥጋችን ላይ ይሠራ ነበር። 6አሁን ግን ቀድሞ ጠፍሮ አስሮን ለነበረው ሞተን፣ ከሕግ ነጻ ወጥተናል፤ ይህም አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ አዲስ በሆነው በመንፈስ መንገድ እንድናገለግል ነው።
ከኀጢአት ጋር መታገል
7እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ በራሱ ኀጢአት ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ፣ ኀጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ፣ ምኞት ምን እንደሆነ በርግጥ አላውቅም ነበር። 8ኀጢአት ግን ትእዛዙ ባስገኘው ዕድል ተጠቅሞ በእኔ ውስጥ ማንኛውንም ዐይነት አጒል ምኞት አስነሣ፤ ኀጢአት ያለ ሕግ ምዉት ነውና። 9ሕጉ ሳይኖር ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ ከመጣ በኋላ ግን፣ ኀጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትሁ። 10ለሕይወት እንዲሆን የታሰበው ያ ትእዛዝም ሞትን እንዳመጣ ተገነዘብሁ፤ 11ኀጢአት በትእዛዝ በኩል የተገኘውን ዕድል በመጠቀም አታለለኝ፤ በትእዛዝም ገደለኝ። 12ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና መልካም ነው።
13ታዲያ በጎ የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? ከቶ አይደለም፤ ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ፤ ይኸውም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት ይሆን ዘንድ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 1:21-25
21በእርሱም አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ፤ ስለዚህ እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው።
22እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ፣ ለወንድሞቻችሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር፣ በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር ነው። 24ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል፣
“ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤
ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።
ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤
25የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”
የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።
ወንጌል
ማቴዎስ 6:25-34
አለመጨነቅ
25“ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? 26እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? 27ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?
28“ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። 29ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም። 30እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? 31ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ 32አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያ ስፈልጓችሁ ያውቃል። 33ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል። 34ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና”።