October 1 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 10:10-31
10ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጒረምርሙ።
11ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ። 12ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
ከጣዖት ጋር አለመተባበር
14ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። 15ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ። 16የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? 17እንጀራው አንድ እንደሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።
18እስቲ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? 19ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን? 20አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋር እንድት ተባበሩም አልሻም። 21የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማእድና ከአጋንንት ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም። 22ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከእርሱ እንበልጣለንን?
የአማኞች ነጻነት
23“ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉም ነገር ተፈቅዶአል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አያን ጽም። 24እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ።
25በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ፣ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤ 26ምድርና በውስጧ ያለው ሁሉ የጌታ ነውና።
27የማያምን ሰው ጋብዞአችሁ ለመሄድ ብትፈልጉ በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ። 28ነገር ግን አንዱ፣ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ፣ ይህን ስለ ነገራችሁ ሰውና ለኅሊናችሁ ስትሉ አትብሉ። 29ይህን የምለውም ስለዚያ ሰው ኅሊና እንጂ ስለ አንተ አይደለም፤ ነጻነቴስ በሌላ ሰው ኅሊና ለምን ይመዘን? 30ምግቡን በምስጋና የምበላ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን ባመሰገንሁበት ነገር ለምን እወቀሣለሁ?
31እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 4:1-11
ለእግዚአብሔር መኖር
1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።
7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤ 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል
ማርቆስ 8:27-38
ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የነበረው ግንዛቤ
27ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።
28እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት።
29ቀጥሎም፣ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው።
30ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።
ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ
31ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር።
32እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።
33ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው።
34ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ 35ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። 36ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? 37ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? 38በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”