October 25 2020

የመጀመሪያ ምንባብ

ኤፌ 6፡ 1~19

ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር

ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። እናንተም

አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። ባሪያዎች ሆይ፥

ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤

የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ

የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም

ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና።

እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ

በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና። በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ

ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።

መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር

በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥

ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን

በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው

ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን

የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።

በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት

ሁሉ ትጉ፤ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ

ለምኑ፤

ሁለተኛ ምንባብ

ራዕ 12፡ 1~12

ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ

ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ

ተጭንቃ ጮኸች። ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም

ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው።

ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም ሁሉ

በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ

ተነጠቀ። ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ

ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች። በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም

ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም

ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር

ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል። አሁን የአምላካችን

ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው

የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥

ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም። ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤

ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ

ወርዶአልና።

የወንጌል ምንባብ

ሉቃ 12፡ 16~31

ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል። አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም። ፍሬዬን

የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ

ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም። አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ

ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን።

አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል?

አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ለደቀ

መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ

በምትለብሱት አትጨነቁ። ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም

አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች

እንዴት ትበልጣላችሁ? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ

ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ

ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ

አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር

እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም

የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ

ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ

ይጨመርላችኋል።

Previous
Previous

November 1 2020

Next
Next

October 18 2020