October 20 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
1 ቆሮንቶስ 10:1-18
በእስራኤል የደረሰው እንዳይደርስብን እንጠንቀቅ
1ወንድሞች ሆይ፤ አባቶቻችን ሁሉ ከደመናው በታች እንደ ነበሩና በባሕሩ ውስጥ እንደ ተሻገሩ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ። 2እነርሱ ሁሉ ከሙሴ ጋር ለመተባበር በደመናና በባሕር ተጠመቁ። 3ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ 4ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ ዐለት ክርስቶስ ነበረ። 5ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በብዙዎቹ ደስ ስላል ተሰኘ በበረሓ ወድቀው ቀሩ።
6እነርሱ ክፉ እንደ ተመኙ፣ እኛም ደግሞ እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆነውልናል። 7“ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ። 8ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሃያ ሦስት ሺህ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም። 9ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑና በእባብ ተነድፈው እንደ ጠፉ፣ እኛም ጌታን አንፈታተን። 10ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጒረምርሙ።
11ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ። 12ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።
ከጣዖት ጋር አለመተባበር
14ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። 15ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ። 16የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? 17እንጀራው አንድ እንደሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።
18እስቲ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን?
ሁለተኛ ምንባብ
ራእይ 14:1-5
በጉና መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች
1ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ። 2ከሰማይ እንደ ብዙ ውሃ ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁት ድምፅ በገና ደርዳሪዎች እንደሚደረድሩት ዐይነት ነበረ። 3እነርሱም በዙፋኑ ፊት፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጡራንና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ መዝሙር ዘመሩ። ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች በስተቀር መዝሙሩን ማንም ሊማረው አልቻለም። 4እነዚህ ራሳቸውን በሴቶች ያላረከሱት ናቸው፤ ራሳቸውን በንጽሕና ጠብቀዋልና። በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው። 5በአፋቸው ምንም ዐይነት ውሸት አልተገኘም፤ ነቀፋም የለባቸውም።
ወንጌል
ማቴዎስ 12:1-21
ሰንበትን ስለ ማክበር
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር። 2ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን መደረግ የሌለበትን እያደረጉ ነው” አሉት።
3እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? 4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባ፤ ለካህናት እንጂ ለእርሱም ሆነ አብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት በላ። 5ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም? 6ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ። 7‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። 8የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”
9ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤ 10በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዶአል?” ብለው ጠየቁት።
11እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጎትቶ አያወጣውምን? 12ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል” አላቸው።
13ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላኛውም እጁ ደህና ሆነለት። 14ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።
እግዚአብሔር የመረጠው አገልጋይ
15ኢየሱስ ሐሳባቸውን አውቆ ከዚያ ዘወር አለ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤ 16ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። 17ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤
18“እነሆ የመረጥሁት፣
የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣
መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤
እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል።
19አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤
ድምፁም በአደባባይ አይሰማም።
20ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣
የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤
የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም።
21አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”