October 15 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ኤፌሶን 6:1-9
ወላጆችና ልጆች
1ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። 2“አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ 3“መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ነው።
4አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።
ጌቶችና ባሪያዎች
5ባሪያዎች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምት ታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በልብ ቅንነትም ታዘዙ፤ 6ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው። 7ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤ 8ምክንያቱም፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።
9እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።
ሁለተኛ ምንባብ
ራእይ 12:1-12
ሴቲቱና ዘንዶው
1ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሓይን የለበሰች፣ ጨረቃን ከእግሮቿ በታች የረገጠችና በራሷም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል የደፋች አንዲት ሴት ታየች። 2እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድ ስትል ምጥ ይዞአት ተጨንቃ ጮኸች። 3ከዚያም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት አክሊል የደፋ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ። 4ጅራቱ የከዋክብትን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ እርሷም በወለደች ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ዘንዶው ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ። 5ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። 6ሴቲቱም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ክብካቤ እንዲደረግላት እግዚአብሔር ወዳ ዘጋጀላት ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።
7በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ 8ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። 9ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።
10ከዚህ በኋላ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና
መንግሥት፣
የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቶአል።
ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው
የነበረው፣
የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።
11እነርሱም በበጉ ደም፣
በምስክርነታቸውም ቃል፣
ድል ነሡት፤
እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣
ለነፍሳቸው አልሳሱም።
12ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣
በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣
ደስ ይበላችሁ፤
ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ
እንደ ቀረው ስላወቀ፣
በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።
ወንጌል
ሉቃስ 12:16-31
16ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤ 17ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።
18“እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’
20“እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊውስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው።
21“ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”
አትጨነቁ
22ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ 23ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? 25ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማነው? 26እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ?
27“እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። 28እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? 29ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ በመሻት ልባችሁ አይጨነቅ፤ 30ይህንማ በዓለም ያለ ሕዝብ ሁሉ ይፈልጋል፤ አባታችሁ እኮ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል። 31ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ በተጨማሪ ይሰጣችኋል።