October 9 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

ኤፌሶን 5:21-33
21
ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።

ባልና ሚስት

22ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ 23ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። 24እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል።

25ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ 26በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ 27እንዲሁም ጒድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። 28ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። 29የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ 30እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና። 31“ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ”። 32ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው፤ እኔም ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ። 33ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር።

ሁለተኛ ምንባብ

ራእይ 21:1-8
አዲሲቱ ኢየሩሳሌም

1ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። 2ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። 3ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። 4እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”

5በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ፤ ደግሞም፣ “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለ።

6እንዲህም አለኝ፤ “ተፈጸመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ። 7ድል የሚነሣ ይህን ሁሉ ይወርሳል፤ እኔም አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። 8ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኵሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”

ወንጌል

ዮሐንስ 3:25-36
25
በአንዳንድ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአንድ አይሁዳዊ መካከል ስለ መንጻት ሥርዐት ክርክር ተነሣ፤ 26ወደ ዮሐንስም መጥተው፣ “ረቢ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው፣ እነሆ ያጠምቃል፤ ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሄደ ነው” አሉት።

27ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም። 28‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ’ እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። 29ሙሽራዪቱ የሙሽራው ነች፤ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን፣ የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሞአል። 30እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል።

31“ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ 32ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ማንም አይቀበልም፤ 33ምስክርነቱንም የተቀበለ ሰው፣ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ አረጋገጠ። 34እግዚአብሔር መንፈሱን ሳይሰፍር ስለሚሰጥ፣ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። 35አብ ወልድን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል። 36በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።”

Previous
Previous

October 16 2022

Next
Next

October 2 2022