November 7 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 11:13-24
13
አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤ 14ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው። 15የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? 16በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።

17ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘውን በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣ 18በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኵራራ። ብትኰራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ ግን አንተን ይሸከምሃል እንጂ። 19እንግዲህ፣ “ቅርንጫፎች የተሰበሩት እኔ እንድገባ ነው” ትል ይሆናል። 20ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን። 21እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው፣ ለአንተም አይራራልህምና።

22እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭካኔ ተመልከት፤ ጭካኔውም በወደቁት ላይ ነው፤ ቸርነቱ ግን በቸርነቱ ውስጥ እስካለህ ድረስ ለአንተ ነው፤ ያለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ። 23እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ፣ ተመልሰው ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያስገባቸው ይችላልና። 24የበረሓ ከሆነው የወይራ ዛፍ የተቈረጥህና ተፈጥሮህ ወዳልሆነው ወደ መልካሙ ወይራ የገባህ ከሆንህ፣ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት እነዚህ ወደ ራሳቸው ወይራ ዛፍ መግባታቸውማ ምን ያህል ይሆን?

ሁለተኛ ምንባብ

ራእይ 12:13-17
13
ዘንዶው ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ፣ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። 14ሴቲቱም በበረሓ ወደ ተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል ሁለት የታላቁ ንስር ክንፎች ተሰጣት፤ ይህም የሆነው በዚያ ከእባቡ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በክብካቤ እንድትኖር ነው። 15እባቡም ሴቲቱ በጐርፍ ተጠራርጋ እንድትወሰድ፣ እንደ ወንዝ ያለ ውሃ ከአፉ ተፋ። 16ምድር ግን ሴቲቱን ረዳቻት፤ አፏንም ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠች። 17ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው።

ወንጌል

ማቴዎስ 21:33-46
የወይን ዕርሻ ገበሬዎች ምሳሌ

33“ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የወይን ዕርሻ ባለቤት ነበረ፤ በዕርሻው ዙሪያ አጥር አጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 34የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው።

35“ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። 36እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። 37በመጨረሻም፣ ‘ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ።

38“ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። 39ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት።

40“ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?”

41እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት።

42ኢየሱስም እንዲህ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን? አላቸው፤

“ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

የማእዘን ራስ ሆነ፤

እግዚአብሔር ይህን አድርጎአል፤

ሥራውም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’

43“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ 44በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ የሚወድቅበት ሰው ግን ይደቅቃል።”

45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። 46ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።

Previous
Previous

November 14 2021

Next
Next

October 31 2021