May 7 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ቈላስይስ 3:1-25
የቅድስና ሕይወት መመሪያ
1እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ 2አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። 3ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሮአልና፤ 4ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።
5ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። 6በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ 7እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ 8አሁን ግን ቊጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ 9አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። 10የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ 11በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
12እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደመሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ 13እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። 14በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።
15እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። 16የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። 17በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
የክርስቲያናዊ ቤተ ሰብ መመሪያ
18ሚስቶች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ለባሎቻችሁ ታዘዙ።
19ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው።
20ልጆች ሆይ፤ ይህ ጌታን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ ለወላጆቻችሁ በሁሉም ነገር ታዘዙ፤
21አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው።
22ባሮች ሆይ፤ ሰውን ለማስደሰትና ለታይታ ብላችሁ ሳይሆን በቅን ልብ ጌታን በመፍራት ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ነገር ታዘዙ። 23የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ 24ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው። 25በደለኛውም የእጁን ያገኛል፤ አድልዎም የለም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:15-22
15ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
ወንጌል
ሉቃስ 24:33-44
23ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። 24ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”
25እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ 26ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” 27ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።
28ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። 29እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።
30አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። 31በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።
33በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ 34“እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። 35ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ተገለጠ
36ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።
37እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። 38እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? 39እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”
40ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። 42እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራሽ ሰጡት፤ 43እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።
44እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።