June 16 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ዕብራውያን 1:1-14
ልጁ ከመላእክት በላይ ነው
1እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ 2በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። 3እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። 4ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኗል።
5እግዚአብሔር፣
“አንተ ልጄ ነህ፤
እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤”
ወይስ ደግሞ፣
“እኔ አባት እሆነዋለሁ፤
እርሱም ልጅ ይሆነኛል”
ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 6ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣
“የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል።
7ስለ መላእክትም ሲናገር፣
“መላእክቱን ነፋሳት፣
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል።
8ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤
“አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤
ጽድቅም የመንግሥትህ በትር ይሆናል፤
9ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣
የደስታንም ዘይት ቀባህ።”
10ደግሞም እንዲህ ይላል፤
“ጌታ ሆይ፤ አንተ
በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤
ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው።
11እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤
ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤
12እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤
እንደ ልብስም ይለወጣሉ።
አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤
ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”
13እግዚአብሔር፣
“ጠላቶችህን የእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ”
ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 14መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 3:18-22
18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው። 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እንቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
ወንጌል
ማርቆስ 16:14-20
14ከዚያም ዐሥራ አንዱ በማእድ ላይ ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች የነገሯቸውን ስላላመኗቸው፣ አለማመናቸውንና የልባቸውን ድንዳኔ ነቀፈ። 15እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ 16ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 17የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ 18እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።”
19ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 20ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።