May 16 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
2ኛ ቆሮንጦስ 5፡11-21
የማስታረቅ አገልግሎት
እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እንጥራለን። የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠ ነው፤ ደግሞም በኅሊናችሁ ዘንድ ግልጽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን የምለው ራሳችንን በእናንተ ፊት እንደ ገና ለማመስገን ሳይሆን፣ በእኛ እንድትመኩ ዕድል ልሰጣችሁ ነው፤ ይኸውም በውጭ በሚታየው ለሚመኩት እንጂ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ለማይመኩ መልስ መስጠት እንድትችሉ ነው። ከአእምሮ ውጪ ብንሆን ለእግዚአብሔር ብለን ነው፤ ባለ አእምሮም ብንሆን ለእናንተ ነው። የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል። በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በውጫዊ ነገር አንመዝንም፤ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን በዚህ መልክ መዝነነው ነበር፤ ከእንግዲህ ግን እንደዚህ አናደርግም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ አዲስ ሆኖአል። ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን፤ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር፤ ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን። ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።
ሁለተኛ ምንባብ
2ኛ ጴጥሮስ 3፡ 14-18
ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፎአል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ፤ ለእርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን፤ አሜን።
የወንጌል ምንባብ
ሉቃስ 24፡ 13-35
በኤማሁስ መንገድ ላይ በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር። እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት እርሱም፣
“የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ። አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።