May 12 2024

የመጀመሪያ ምንባብ

ወደ ዕብራውያን 9:1-10

ሰማያዊው አገልግሎት ከምድራዊው አገልግሎት እንደሚበልጥ

1የመጀመሪያው ኪዳን የአገልግሎት ሥርዓትና ምድራዊ መቅደስ ነበራት። 2ድንኳን ተዘጋጅቶ ነበር፥ በእርስዋም ውስጥ ቅድስት በምትባለው መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበር። 3ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፤ 4በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበር፤ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት፥ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ። 5በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበር፤ ስለ እነዚህም በዝርዝር የመናገሪያው ሰዓት አሁን አይደለም።

6 ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ እያለ ካህናት የአምልኮ አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ደጋግመው ይገቡባታል፤ 7በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ 8በዚህ መንገድ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ እያለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። 9ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ሲሆን፥ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም የማያደርጉ፥ 10ነገር ግን ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ የመንጻት ሥርዓቶች የሚውሉ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ስለ ሆኑ፥ እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ ናቸው።

ሁለተኛ ምንባብ

የዮሐንስ ራእይ 12: 1-10
ሴቲቱና ዘንዶው

1ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የለበሰች፥ ጨረቃን ከእግሮችዋ በታች ያደረገች፥ ባለ ዐሥራ ሁለት ኮከቦች አክሊልም በራስዋ ላይ የደፋች አንዲት ሴት ነበረች። 2እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድም ምጥ ይዟት ተጨንቃ ትጮኻለች። 3ሌላም ምልክት በሰማይ ተከሠተ፤ እነሆ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፤ 4በጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ከዚያም ዘንዶው ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ሕፃንዋን ለመዋጥ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ። 5አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። 6ሴቲቱም ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደነበረው ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።

7 በሰማይም ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ 8አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። 9ታላቁም ዘንዶ ወደ ታች ተጣለ፤ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። 10ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ፤ እንዲህ ሲል
“አሁን የአምላካችን ማዳን፥ ኃይልም፥ መንግሥትም እንዲሁም የክርስቶስ ሥልጣን ሆነ፤
ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።

የሐዋርያት ሥራ 2:22-36

22“የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁት፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ 23እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዐመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። 24እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፤ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። 25ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና

“ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።

26ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፤

ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤

27ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህንም

መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። 28የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤

ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።”

29ወንድሞች ሆይ! ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። 30ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደማለለት ስለ አወቀ፥ 31ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። 32ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ 33ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ነገር ግን እርሱ እንዳለው፦

ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፤

35“ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ!”

36“እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።”

ወንጌል

ሉቃስ 1:39-56
ማርያምና ኤልሳቤጥ

39ማርያምም በእነዚያ ቀናት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር በይሁዳ ወደምትገኝ ከተማ ፈጥና ሄደች፤ 40ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ 42በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? 44እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። 45ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።”

የማርያም የምስጋና ጸሎት

46ማርያምም እንዲህ አለች፦

“ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤

47መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤

48 እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና።

እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤

49ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤

ስሙም ቅዱስ ነው።

50ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል።

51በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤

በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤

52 ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤

ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤

53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤

ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።

54እስራኤልን አገልጋዩን፥

ምሕረቱን በማስታወስ፥

55 ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም እንደ ተናገረው ረድቶአል።”

56ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚያም ወደ ቤትዋ ተመለሰች።

Previous
Previous

May 19 2024

Next
Next

May 4 2024