May 09 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

1ኛ ቆሮንጦስ 15፡1-19
አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክ ሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቈጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፣ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው።

የሙታን ትንሣኤ

ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢ አታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ዮሐንስ 1፡ 1-10
የሕይወት ቃል

ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዐይኖቻችን ያየነውን፣ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን። ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክርለታለንም። በአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠልንን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤ እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ፣ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን፤ ኅብረታችንም ከአብ፣ ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ደስታችንም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን።

በብርሃን መመላለስ

ከእርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው። በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም። ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

የወንጌል ምንባብ

ዮሐንስ 20፡ 19-31
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 20ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ 23የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

ኢየሱስ ለቶማስ ታየ

24በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት። እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ። ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 27ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው። ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው። ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።

Previous
Previous

May 16 2021

Next
Next

May 9 2021