May 02 2021
የመጀመሪያ ምንባብ
1ኛ ቆሮንጦስ 15፡20-34
ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ “ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሎአልና፤ ነገር ግን፣ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፣ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። በኤፌሶን ከአራዊት ጋር የታገልሁት ለሰው አስተያየት ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው። አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
1ኛ ጴጥሮስ 1፡ 1-12
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኝነት ለሚኖሩ ለእግዚአብሔር ምርጦች፤ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ሕያው ስለ ሆነው ተስፋ ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን። እናንተም በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እውነተኛ መሆኑ እንደተረጋገጠና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል፤ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና። ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤ በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ባበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ።
የወንጌል ምንባብ
ዮሐንስ 20፡ 1-18
በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። “ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።
ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ
10ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት። እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ
በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው።