June 30 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 5:12-21
ሞት በአዳም፣ ሕይወት በክርስቶስ
12ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ 13ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። 14ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ።
15ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! 16ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!
18ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። 19በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።
20ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ 21ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።
ሁለተኛ ምንባብ
3 ዮሐንስ 1:1-15
1ሽማግሌው፤
በእውነት ለምወድደው ለውድ ወዳጄ ለጋይዮስ፤
2ወዳጅ ሆይ፤ ነፍስህ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለች ሁሉ መልካም ጤንነት እንዲኖርህና በነገር ሁሉ እንዲሳካልህ እጸልያለሁ። 3ለእውነት ታማኝ እንደ ሆንህና የምትመላለሰውም በእውነት እንደ ሆነ አንዳንድ ወንድሞች መጥተው ስለ አንተ ሲመሰክሩልኝ እጅግ ደስ አለኝ። 4ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም።
5ወዳጅ ሆይ፤ ለአንተ እንግዶች ቢሆኑም እንኳ፣ ለወንድሞች በምታደርገው ነገር ሁሉ ታማኝ ነህ። 6እነርሱ አንተ ስላለህ ፍቅር በቤተ ክርስቲያን ፊት መስክረዋል፤ በመንገዳቸውም እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ ብትረዳቸው መልካም ታደርጋለህ፤ 7ስለ ስሙ የወጡት ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ ነውና። 8እንግዲህ አብረን ለእውነት እንድንሠራ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ልናስተናግድ ይገባናል።
9ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ መሆን የሚወድደው ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። 10ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ፤ ይህም አልበቃ ብሎት ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሏቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፤ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል።
11ወዳጅ ሆይ፤ መልካም የሆነውን እንጂ ክፉውን አትምሰል። መልካም የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። ክፉ የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። 12ለድሜጥሮስ፣ ሰው ሁሉ ይመሰክርለታል፤ እውነት ራሷም ትመሰክርለታለች፤ እኛ ደግሞ እንመሰክርለታለን፤ እናንተም ምስክርነታችን እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።
13የምጽፍልህ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በቀለምና በብርዕ እንዲሆን አልፈልግም። 14በቅርቡ ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ፊት ለፊትም እንነጋገራለን።
15ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለወዳጆች በየስማቸው ሰላምታ አቅርብልኝ።
ወንጌል
ማቴዎስ 22:1-22
በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ
1ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ 2“መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥ ትመስላለች፤ 3ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ።
4“እንደ ገናም ሌሎች አገልጋዮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን አርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ።
5“ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6የቀሩትም አገልጋዮቹን በመያዝ አጉላልተው ገደሏቸው። 7ንጉሡም በመቈጣት ሠራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።
8“ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ 9ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ 10አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።
11“ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ 12እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም።
13“ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ 14የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”
ግብር ስለ መክፈል
15ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ እላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። 16ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋር ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደሆንህ፣ ለማንም ሳታዳላ ሁሉን በእኩልነት እንደምትመለከት እናውቃለን፤ 17ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”
18ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? 19ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። 20እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።
21እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት።
እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።
22ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።