June 12 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 15:20-40
20
ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። 21ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። 22ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ 23ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። 24ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። 25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 26የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ 27“ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሎአልና፤ ነገር ግን፣ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፣ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። 28ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።

29ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? 30እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? 31ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። 32በኤፌሶን ከአራዊት ጋር የታገልሁት ለሰው አስተያየት ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፤

“ነገ ስለምንሞት፣

እንብላ፣ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው።

33አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” 34ወደ ሰከነ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና ይህንንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው።

የትንሣኤ አካል

35ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። 36አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። 37የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። 38እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። 40እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 3:15-22
15
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።

ወንጌል

ሉቃስ 22:31-46
31
ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ 32እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”

33ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋር ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው።

34ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው።

35ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ።

36እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ። 37እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሶአል።”

38ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት።

እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።

ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ጸለየ

39ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 40እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤ 42እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” 43መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። 44እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር።

45ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣ 46“ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው።

Previous
Previous

June 19 2022

Next
Next

June 5 2022