July 25 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ጢሞቴዎስ 4:1-16
1
በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እንደሚከተሉ መንፈስ በግልጥ ይናገራል። 2እንዲህ ያለው ትምህርት የሚመጣው ኅሊናቸው በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል ከደነዘዘባቸው ግብዝ ውሸተኞች ነው። 3እነርሱ፣ ሰዎች እንዳያገቡ ይከለክላሉ፤ የሚያምኑና እውነትን የሚያውቁ ሰዎች እግዚአብሔር የፈጠረውን በምስጋናም የሚቀበሉትን እንዳይበሉ ያዛሉ፤ 4እግዚአብሔር የፈጠረው ማንኛውም ነገር መልካም ነውና፤ በምስጋና ከተቀበሉትም የሚጣል ምንም ነገር የለም፣ 5በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።

6ይህን ትእዛዝ ለወንድሞች ብታሳስብ፣ በእምነት ቃልና በተቀበልኸው መልካም ትምህርት ታንጸህ የክርስቶስ ኢየሱስ በጎ አገልጋይ ትሆናለህ። 7እግዚአብሔርን ከማያከብር ርባናቢስ አፈ ታሪክና ከአሮጊቶች ተረታ ተረት ራቅ፤ ይልቁንም ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን አሠልጥን። 8የአካል ብቃት ልምምድ ለጥቂት ነገር ይጠቅማልና፤ ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስን ማሠልጠን ግን ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁለቱም ይጠቅማል።

9ይህ ቃል የታመነና ሙሉ ለሙሉ ሊቀበሉት የሚገባ ነው፤ 10ለዚህ ብለን እንጥራለን፤ እንደክማለንም፤ ይኸውም ለሰዎች ሁሉ በተለይም ለሚያምኑት አዳኝ በሆነው በሕያው እግዚአብሔር ተስፋ ስለምናደርግ ነው።

11እነዚህን ነገሮች እዘዝ፤ አስተምርም። 12ወጣትነትህን ማንም አይናቅ፤ ነገር ግን ለሚያምኑት በንግግርና በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርኣያ ሁንላቸው። 13እኔ እስክመጣ ድረስ ለማንበብ፣ ለመምከርና ለማስተማር ትጋ። 14ሽማግሌዎች እጃቸውን በአንተ ላይ ሲጭኑ በትንቢት የተሰጠህን የጸጋ ስጦታቸል አትበል።

15ሰው ሁሉ ማደግህን ያይ ዘንድ በእነዚህ ነገሮች ላይ አትኵር፤ በትጋትም ፈጽማቸው፤ 16ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህና።

 

ሁለተኛ ምንባብ

2 ጴጥሮስ 1:12-18
የቅዱሳት መጻሕፍት ትንቢት

12ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸ ኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። 13በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጐትጐት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ 14ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ 15እነዚህን ነገሮች ከተለየኋችሁም በኋላ ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ።

16ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ እኮ የእርሱን ግርማ በዐይናችን አይተን እንጂ፣ በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም፤ 17ምክንያቱም ከግርማዊው ክብር “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርና ሞገስ ተቀብሎአል፤ 18እኛም ከእርሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል።

ወንጌል

ሉቃስ 6:1-19
1
በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። 2ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው።

3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? 4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኀብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” 5ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።

6በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። 7ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። 8ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካካል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ።

9ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።

10ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። 11ሰዎቹ ግን በቊጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ

12ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። 13ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ 14እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ 15ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፤ 16የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ።

የቡራኬና የወዮታ ስብከት

17ኢየሱስም አብሮአቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፣ 18እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ 19ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።

Previous
Previous

August 01 2021

Next
Next

July 25 2021