July 21 2024

የመጀመሪያ ምንባብ

2 ቆሮንቶስ 10:1-18

ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ያቀረበው መከላከያ

1እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ። 2ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በዓለማዊ መንገድ እንደምንኖር አድርገው በሚቈጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር ቈርጫለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ዐይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። 3የምንኖረው በዚህ ዓለም ቢሆንም፣ የምንዋጋው በዚህ ዓለም ስልት አይደለም። 4ደግሞም የምንዋጋበት የጦር መሣሪያ የዚህ ዓለም መሣሪያ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደምሰስ የሚችል መለኮታዊ ኀይል ያለው ነው። 5በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን። 6መታዘዛችሁ በተፈጸመ ጊዜ አለ መታዘዝን ሁሉ ለመቅጣት ተዘጋጅተናል።

7እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም የክርስቶስ በመሆኑ ቢመካ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን ሊገነዘብ ይገባዋል። 8ጌታ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበል ነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና። 9በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። 10አንዳንዶች፣ “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይላሉ። 11እንዲህ የሚሉ ሰዎች በሩቅ ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን ሁሉ በቅርብ ሆነን በተግባራችን የምንገልጸውም እንደዚያው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።

12ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንመድብ ወይም ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመ ዝኑና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያነጻ ጽሩ አስተዋዮች አይደሉም። 13እኛ ግን ከመጠን በላይ አንመካም፤ የምንመካው እግዚአብሔር በመደበልንና እስከ እናንተም እንኳ በሚደርሰው የአገልግሎታችን ወሰን ነው። 14የክርስቶስን ወንጌል ይዘን ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ፣ ከተመደበልን የአገልግሎት ወሰን አላለፍንም። 15ደግሞም ሌሎች በደከሙበት ሥራ ከመጠን በላይ በመመካት ከተመደበልን ወሰን አናልፍም፤ ይልቁንም እምነታችሁ እያደገ በሄደ ቍጥር በእናንተ ዘንድ የተመደበልን አገልግሎት እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን። 16ስለዚህ በሌላው ሰው ክልል አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ሳንመካ፣ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር ወንጌልን መስበክ እንችላለን። 17ነገር ግን፣ “የሚመካ በጌታ ይመካ”፤ 18ምክንያቱም ጌታ ራሱ የሚያመሰግነው እንጂ፣ ራሱን በራሱ የሚያመሰግን ተቀባይነት አይኖረውም።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 3:1-8

አንደበትን መግታት

1ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ። 2ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።

3ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። 4ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። 5እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ 6ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች።

7ማናቸውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። 8ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት።

ወንጌል

ማቴዎስ 8:1-34

የለምጻሙ መንጻት

1ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 2እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው።

3ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። 4ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው።

የመቶ አለቃው እምነት

5ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ 6“ጌታ ሆይ፤ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቶአል” አለው።

7ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።

8የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል፤ 9እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።”

10ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ 11እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ማእድ ዙሪያ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ይቀመጣሉ፤ 12መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

13ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።

ኢየሱስ ብዙዎችን መፈወሱ

14ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጎራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታማ ተኝታ አገኛት። 15እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው።

16በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። 17በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤

“እርሱ ደዌያችንን ተቀበለ፤

ሕመማችንንም ተሸከመ።”

የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ውሳኔ ይጠይቃል

18ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው። 19በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።

20ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት።

21ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው።

22ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው።

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ

23ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። 24ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። 25ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ! ጠፋን፤ አድነን” አሉት።

26ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ።

27ሰዎቹም፣ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።

ከርኩሳን መናፍስት ስለ ተፈወሱ ሁለት ሰዎች

28ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። 29እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።

30ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 31አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። 32ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። አጋንንቱም ከሰዎቹ ወጥተው ዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹም በሙሉ ከነበሩበት አፋፍ እየተጣደፉ ባሕሩ ውስጥ በመግባት ውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። 33የዐሣማዎቹ ጠባቂዎችም ሸሽተው ወደ ከተማ በመሄድ፣ የሆነውን ሁሉና በአጋንንት ተይዘው በነበሩት ሰዎች ላይ የተደረገውን ነገር አወሩ። 34እነሆም፤ መላው የከተማ ነዋሪ ኢየሱስን ለመገናኘት ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ለመኑት።

Previous
Previous

July 28 2024

Next
Next

July 14 2024