January 7 2025

የመጀመሪያ ምንባብ

ገላትያ 4:1-1
1
እኔ የምለው ይህ ነው፤ ወራሹ ሕፃን እስከ ሆነ ድረስ፣ ሀብት ሁሉ የእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ከባሪያ የተለየ አይደለም። 2አባቱ እስከ ወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በሞግዚቶች ሥር ነው። 3እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከዓለም መሠረታዊ ትምህርት ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር። 4ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው። 6ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።

7ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።

ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ማሰቡ

8እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ 9አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በእርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን? 10ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ። 11ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።


ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 4:9-21
9እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በእርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ። 10ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኀጢአታችን ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው። 11ወዳጆች ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ከወደደን፣ እኛም እርስ በእርሳችን መዋደድ ይገባናል። 12እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።

13መንፈሱን ስለ ሰጠን፣ እኛ በእርሱ እንደምንኖር እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን። 14አብ ልጁን የዓለም አዳኝ ይሆን ዘንድ እንደላከው ዐይተናል፤ እንመሰክራለንም። 15ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። 16ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን።

እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 17በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና። በፍርድ ቀን ድፍረት ይኖረን ዘንድ፣ ፍቅር በዚህ ዐይነት በመካከላችን ፍጹም ሆኖአል፤ 18በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።

19እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 20ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና። 21እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።

ወንጌል

ሉቃስ 2:1-20
የኢየሱስ መወለድ

1በዚያን ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። 2ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዢ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር። 3ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።

4ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ። 5ወደዚያም ለመመዝገብ የተጓዘው፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር። 6በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤ 7የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው።

እረኞችና መላእክት

8በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። 9የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው። 10መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና። 11ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። 12ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።”

13ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤

14“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ

ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”

15መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ።

16እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። 17ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። 18ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ 19ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። 20እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።

Previous
Previous

January 12 2025

Next
Next

January 5 2025