March 31 2024
የመጀመሪያ ምንባብ
ገላትያ 5:1-26
1ክርስቶስ ነጻ ያወጣን በነጻነት እንድንኖር ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ።
2የምለውን አስተውሉ፤ ትገረዙ ዘንድ ብትፈልጉ፣ ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንት እንደማይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችኋለሁ። 3መገረዝ ለሚፈልግ ሁሉ ሕግን በሙሉ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት እንደ ገና ለእያንዳንዱ በግልጽ እናገራለሁ። 4በሕግ ለመጽደቅ የምትጥሩ፣ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋ ርቃችኋል። 5እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን ጽድቅ፣ በመንፈስ አማካይነት በእምነት ሆነን በናፍቆት እንጠባበቃለን። 6በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑ፣ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፤ የሚጠቅመውስ በፍቅር የሚገለጽ እምነት ብቻ ነው።
7ሩጫችሁ መልካም ነበር፤ ታዲያ ያሰናከላችሁ፣ ለእውነትስ እንዳትታዘዙ የከለከላችሁ ማን ነው? 8እንዲህ ያለው ማባበል ከሚጠራችሁ የመጣ አይደለም፤ 9“ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።” 10የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ በጌታ እታመናለሁ። ግራ የሚያጋባችሁ ማንም ይሁን ማን፣ ፍርዱን ይቀበላል።
11ወንድሞች ሆይ፤ እስከ ዛሬ ስለ መገረዝ የምሰብክ ከሆነ፣ ታዲያ እስከ አሁን ለምን ያሳድዱኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ፣ መስቀል ዕንቅፋት መሆኑ በቀረ ነበር። 12ግራ የሚያጋቧችሁ ሰዎች የራሳቸውን መግረዝ ብቻ ሳይሆን ይጐንድሉ!
በመንፈስ መመላለስ
13ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል።
14ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሏል፤ ይኸውም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው። 15ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
16እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ እላለሁ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም። 17ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን፣ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን ይመኛልና፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚጋጩ፣ የምትፈልጉትን አታደርጉም። 18በመንፈስ ብትመሩ ግን፣ ከሕግ በታች አይደላችሁም።
19የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ 20ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፤ 21ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው። አስቀድሜ እንዳልሁ፣ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
22የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ 23ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። 24የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። 25በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ። 26እርስ በርሳችን እየተጐነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።
ሁለተኛ ምንባብ
ያዕቆብ 5:14-20
14ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። 15በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል። 16ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል።
17ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም። 18እንደ ገናም ጸለየ፤ ዝናብም ከሰማይ ዘነበ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች።
19ወንድሞቼ ሆይ፤ ከእናንተ አንዱ ከእውነት ቢስትና ሌላው ቢመልሰው፣ 20ይህን አስተውሉ፤ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድነዋል፤ ብዙ ኀጢአትንም ይሸፍናል።
ወንጌል
ዮሐንስ 5:1-24
በቤተ ሳይዳ የተደረገው ፈውስ
1ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። 3በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ ዐንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣ 4ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] 5በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። 6ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው።
7ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው።
8ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። 9ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ።
ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። 10አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለሆነ መተኛህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት።
11እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው።
12እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት።
13ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደ ፈወሰው አላወቀም።
14ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። 15ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው።
ወልድ ሕይወትን ይሰጣል
16አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። 17ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። 18እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።
19ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ 20አብ ወልድን ስለሚወድድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። 21ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። 22አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ 23ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
24“እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። 25እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ 27ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል።