January 16 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 15፡ 1~13
1
እኛ ብርቱዎች የሆን፣ የደካሞችን ጒድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። 2እያንዳንዳችን ባልን ጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል፤

3ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፣ “አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት። 4በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።

5ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ የአንድነትን መንፈስ ይስጣችሁ፤ 6ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።

7እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። 8ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ለእግዚአብሔር እውነት ሲል ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ እንደሆነ እነግራችኋለሁና፤ 9እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤

“ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤

ለስምህም እዘምራለሁ።”

10ደግሞም፣

“አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።

11እንደ ገናም፣

“አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑ፤

ሕዝቦች ሁሉ ወድሱት” ይላል።

12ኢሳይያስም እንዲሁ፣

“በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣

የእሴይ ሥር ይመጣል፤

በእርሱም አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል።

13በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።    

 

ሁለተኛ ምንባብ

1ኛ ዮሐ 4፡ 14~21
14
አብ ልጁን የዓለም አዳኝ ይሆን ዘንድ እንደላከው ዐይተናል፤ እንመሰክራለንም። 15ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። 16ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን።

እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 17በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና። በፍርድ ቀን ድፍረት ይኖረን ዘንድ፣ ፍቅር በዚህ ዐይነት በመካከላችን ፍጹም ሆኖአል፤ 18በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።

19እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 20ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና። 21እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።

ወንጌል

ማቴ 2፡ 19~23
ከግብፅ ወደ ናዝሬት

19ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ 20“ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው።

21ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ 22ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ 23ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።

Previous
Previous

January 19 2022

Next
Next

January 9 2022