February 6 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

ገላትያ 4:21-31
አጋርና ሣራ ምሳሌ መሆናቸው

21እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን? 22አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። 23ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ፣ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነው።

24እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት። 25እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል፣ አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና። 26ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት። 27እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤

“አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤

ደስ ይበልሽ፤

አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣

በእልልታ ጩኺ፤

ባል ካላት ይልቅ፣

የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”

28እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። 29በዚያን ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው፣ ልጅ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው። 30ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከልጇ ጋር አስወግዳት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋር አይወርስምና” ይላል። 31ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 2:1-8
1
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ፤ 2በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።

ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ

4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣ 5እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ። 6ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤

“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣

በጽዮን አኖራለሁ፤

በእርሱም የሚያምን፣ ከቶ አያፍርም።”

7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣

“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”

8ደግሞም፣ “ሰዎችን የሚያሰናክል፣

የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”

የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

ወንጌል

ሉቃስ 2:42-52
42
ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። 43በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። 44አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ 45ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

46ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ 47የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። 48ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

49እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። 50እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም።

51ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። 52ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

Previous
Previous

February 13 2022

Next
Next

January 30 2022