February 11 2024

የመጀመሪያ ምንባብ

ገላትያ 4:21-31
አጋርና ሣራ ምሳሌ መሆናቸው

21እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን? 22አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፏልና። 23ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነው።

24እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት። 25እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና። 26ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት። 27እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤

ደስ ይበልሽ፤

አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣

በእልልታ ጩኺ፤

ባል ካላት ይልቅ፣

የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”

28እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። 29በዚያን ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው ልጅ፣ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው። 30ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከልጇ ጋር አስወግዳት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋር አይወርስምና” ይላል። 31ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 2:1-8
1እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። 2በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።

ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ

4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣ 5እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ። 6ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣

በጽዮን አኖራለሁ፤

በእርሱም የሚያምን ከቶ አያፍርም።”

7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣

“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”

8ደግሞም፣

“ሰዎችን የሚያሰናክል፣

የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”

የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

ወንጌል

ሉቃስ 2:42-52
42ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 44እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። 45ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”

የማርያም መዝሙር

46ማርያምም እንዲህ አለች፤

“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤

47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤

48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና።

ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ

ብፅዕት ይሉኛል፤

49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ

ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤

50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ

እስከ ትውልድ ይኖራል።

51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤

በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤

52ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤

ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤

Previous
Previous

February 18 2024

Next
Next

February 4 2024