December 25 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 13:11-14
11
ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቦአልና። 12ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ። 13በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን። 14ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አትመቻቹለት።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 1:1-10
የሕይወት ቃል

1ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዐይኖቻችን ያየነውን፣ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን። 2ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክርለታለንም። በአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠልንን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤ 3እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ፣ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን፤ ኅብረታችንም ከአብ፣ ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 4ደስታችንም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን።

በብርሃን መመላለስ

5ከእርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው። 6በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም። 7ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።

8ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። 10ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

ወንጌል

ዮሐንስ 1:1-18
ቃል ሥጋ ሆነ

1በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። 2እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ።

3ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። 4ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። 5ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም።

6ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። 7ሰዎች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ 8ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። 9ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር።

10እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። 11ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ 12ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። 13እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።

14ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን።

15ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። 16ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ 17ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። 18ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

Previous
Previous

January 1 2023

Next
Next

December 18 2022