August 22 2021

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 8:31-39
31
ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? 32ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? 33እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ 34ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። 35ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ? 36ይህም፣

“ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤

እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን”

ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

37ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። 38ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ 39ከፍታም ይሁን ጥልቀት፣ ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።

ሁለተኛ ምንባብ

2 ዮሐንስ 1:1-13
1
ሽማግሌው፤

በእውነት ለምወዳት እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ለሚወዷት ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ፤ 2በውስጣችን ከሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ከሚሆን እውነት የተነሣ፣ 3ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።

4ከልጆችሽ አንዳንዶቹ ከአብ በተሰጠን ትእዛዝ መሠረት በእውነት ጸንተው እየሄዱ በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 5አሁንም እመቤት ሆይ፤ ከመጀመሪያ የነበረችውን እንጂ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍልሽም፤ ይኸውም እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ ነው። 6ይህም ፍቅር፤ በትእዛዛቱ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው። ትእዛዙም ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁት በፍቅር እንድትኖሩ ነው።

7ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 8እናንተም የደከማች ሁበትን ዋጋ እንዳታጡ፣ ነገር ግን ሙሉ ሽልማት እንድትቀበሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው። 10ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፣ ይህንንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፤ ሰላምም አትበሉት፤ 11የሚቀበለው ሰው፣ የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና።

12የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ይሁን እንጂ በወረቀትና በቀለም እንዲሆን አልፈልግም፤ ዳሩ ግን ደስታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት ላነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

13የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።

ወንጌል

ሉቃስ 1፡39-56
ማርያም ኤልሳቤጥን ጥየቃ ሄደች

39ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ 40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ 42ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 44እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና። 45ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”

የማርያም መዝሙር

46ማርያምም እንዲህ አለች፤

“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤

47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤

48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና።

ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ

ብፅዕት ይሉኛል፤

49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ

ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤

50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ

እስከ ትውልድ ይኖራል።

51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤

በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤

52ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤

ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤

53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል፤

ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤

54ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን

እስራኤልን ረድቶአል፤

55ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣

ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”

56ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።

Previous
Previous

August 29 2021

Next
Next

August 15 2021