August 17 2025

የመጀመሪያ ምንባብ

ሮሜ 6:12-23
12
ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። 13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።

የጽድቅ ባሮች

15እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች በመሆናችን ኀጢአት እንሥራን? በጭራሽ አይገባም! 16ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምት ታዘዙት ለእርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደሆናችሁ አታውቁምን? 17ነገር ግን የኀጢአት ባሮች የነበራችሁ ቢሆንም፣ ለተሰጣችሁለት ትምህርት በሙሉ ልብ የታዘዛችሁ በመሆናችሁ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ 18ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ፣ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።

19በተፈጥሮ ደካሞች ስለ ሆናችሁ፣ በሰው ቋንቋ ይህን እላለሁ፤ ብልቶቻችሁን በባርነት ለርኵሰትና እየባሰ ለሚሄድ ክፋት ታቀርቡ እንደ ነበር፣ አሁን ደግሞ ወደ ቅድስና ለሚወስደው ጽድቅ ባሪያ አድርጋችሁ አቅርቡ። 20የኀጢአት ባሮች ሳላችሁ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁ። 21አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? የዚያ ነገር ውጤት ሞት ነው። 22አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። 23የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።

ሁለተኛ ምንባብ

ያዕቆብ 4:1-17
ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ

1በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ምኞታችሁ አይደለምን? 2ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም። ትገድላላችሁ፤ በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም። 3ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና።

4አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5ወይስ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? 6ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣

“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤

ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል”

ያለው ስለዚህ ነው።

7እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።

11ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?

ስለ ነገ መመካት

13እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። 14ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ። 15ይልቁንም፣ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። 17እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኀጢአት ያደርጋል።

ወንጌል

ዮሐንስ 7:32-52
32
ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጒምጒ ምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው።

33ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋር የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ 34ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።”

35አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን? 36‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤’ ደግሞም፣ ‘እኔ ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?”

37የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ 38በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” 39ይህን ያለው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀ በሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።

40ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ቃሉን ሰምተው፣ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢዩ ነው” አሉ።

41ሌሎችም፣ “እርሱ ክርስቶስ ነው” አሉ።

ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ሊመጣ ይችላል? 42መጽሐፍ፣ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ ዳዊትም ከኖረበት ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ይናገር የለምን?” 43ስለዚህም በኢየሱስ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ 44አንዳንዶቹም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ማንም እጁን አላሳረፈበትም።

የአይሁድ መሪዎች አለማመን

45በመጨረሻም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ፣ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም ጠባቂዎቹን፣ “ለምን አላመጣችሁትም?” አሏቸው።

46ጠባቂዎቹም፣ “እንደዚህ ሰው፣ ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ።

47ፈሪሳውያንም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተም ተታላችኋል ማለት ነው? 48ለመሆኑ ከባለሥልጣኖችና ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለ? 49ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።”

50ከዚህ ቀደም ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከእነርሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፤ 51“ሕጋችን፣ አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን?”

52እነርሱም፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምር፤ ትደርስበታለህ” ብለው መለሱለት።

Previous
Previous

August 24 2025

Next
Next

August 10 2025