March 30 2025
የመጀመሪያ ምንባብ
2 ጢሞቴዎስ 2:1-15
1እንግዲህ ልጄ ሆይ፤ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። 2በብዙ ምስክር ፊት ከእኔ የሰማኸውን፣ ሌሎችን ለማስተማር ብቃት ላላቸው ለታመኑ ሰዎች ዐደራ ስጥ። 3እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር፣ ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል። 4በውትድርና የሚያገለግል ሰው አዛዡን ለማስደሰት ይጥራል እንጂ በሌላ ሥራ ራሱን አያጠላ ልፍም። 5እንደዚሁም በውድድር የሚሳተፍ ሰው፣ የውድድሩን ሕግ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም። 6ትጉህ ገበሬም ከሰብሉ ለመጠቀም የመጀመሪያው ሊሆን ይገባዋል። 7እኔ የምለውን ልብ በል፤ ጌታ በሁሉም ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና።
8ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው፤ 9ለዚህም እንደ ወንጀለኛ እስከ መታሰር ድረስ መከራን እየተቀበልሁ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። 10ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እነርሱም ያገኙ ዘንድ፣ ለተመረጡት ስል ሁሉንም በመታገሥ እጸናለሁ።
11እንዲህ የሚለው ቃል የታመነ ነው፤
ከእርሱ ጋር ከሞትን፣
ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን።
12ብንጸና፣
ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን።
ብንክደው፣
እርሱ ደግሞ ይክደናል፤
13ታማኞች ሆነን ባንገኝ
እርሱ ታማኝ እንደሆነ ይኖራል፤
ራሱን መካድ አይችልምና።
እግዚአብሔር የተቀበለው ሠራተኛ
14ስለ እነዚህ ነገሮች ማሳሰብህን አትተው፤ በቃላት እንዳይነታረኩ በእግዚአብሔር ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ ጥቅም የሌለው፣ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። 15እንደ ማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሠከረለት ሠራተኛ፣ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ልታቀርብ ትጋ።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ጴጥሮስ 5:1-11
ለሽማግሌዎችና ለጎልማሶች የተሰጠ ምክር
1እንግዲህ ከእነርሱ ጋር እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ 2በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ 3እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን። 4የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ትቀበላላችሁ።
5ጐልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤
ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”
6ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ 7እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
8ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል። 9በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
10በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል። 11ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል
ማቴዎስ 25:14-30
የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ
14“የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ 15ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ። 16አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ 17እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ 18አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።
19“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። 20አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።
21“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
22“እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።
23“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።
24“አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ 25ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።
26“ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሮአል? 27ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።
28“ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ 29ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 30ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።