April 21 2022

የመጀመሪያ ምንባብ

1 ቆሮንቶስ 11:20-29
20
በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን እራት አይደለም፤ 21በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል። 22ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም።

23እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ 24ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ። 25እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። 26ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

27እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል። 28ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤ 29ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣል። 

ሁለተኛ ምንባብ

1 ዮሐንስ 3:18-24
18
ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ። 19እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፣ 20ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል።

21ወዳጆች ሆይ፤ ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን፤ 22ትእዛዛቱንም ስለምንጠብቅና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንቀበላለን። 23ትእዛዙም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንድናምንና እርሱ እንዳዘዘንም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው። 24ትእዛዞቹንም የሚጠብቁ ሁሉ በእርሱ ይኖራሉ፤ እርሱም በእነርሱ ይኖራል። በእኛ መኖሩን በዚህ ይኸውም እርሱ በሰጠን መንፈስ እናውቃለን።

ወንጌል

ማቴዎስ 26:14-30
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ

14ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረውና የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ 15“እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። 16ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን አመቺ ጊዜ ይፈልግ ነበር።

የጌታ ራት

17በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።

18እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። 19ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን ራት አዘጋጁ።

20በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ 21በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።

22እነርሱም እጅግ አዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት።

23እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ 24የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ለዚያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።”

25አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው።

እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው።

26እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው።

27ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ 28ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። 29እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከእንግዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።”

30መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

Previous
Previous

April 22 2022

Next
Next

April 17 2022