April 13 2025

የመጀመሪያ ምንባብ

ዕብራውያን 9:11-28
የክርስቶስ ደም

11ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳ ልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ። 12የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። 13የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ 14በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!

15ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና።

16ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤ 17ምክንያቱም ኑዛዜው የሚጸናው ሰውዬው ሲሞት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ድረስ ኑዛዜው ዋጋ አይኖረውም። 18ስለዚህ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አልነበረም። 19ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፣ ከቀይ የበግ ጠጒርና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ፣ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ 20እንዲህም አለ፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” 21እንዲሁም ድንኳኒቱንና ማገልገያ ዕቃውን ሁሉ በደም ረጨው። 22በርግጥ ከጥቂት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዛል፤ ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና።

23እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት በእነዚህ ነገሮች ሊነጹ ግድ ነበር፤ በሰማይ ያሉት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። 24ክርስቶስ የእውነተኛዪቱ ድንኳን ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደ ተሠራችው መቅደስ አልገባም፤ ነገር ግን አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት፣ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ። 25ሊቀ ካህናት የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ክርስቶስ ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሰማይ አልገባም። 26እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል። 27ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም ተወስኖበታል። 28ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።

ሁለተኛ ምንባብ

1 ጴጥሮስ 4:1-11
ለእግዚአብሔር መኖር

1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።

7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤ 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል

ዮሐንስ 5:11-30
11
እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው።

12እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት።

13ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደፈወ ሰው አላወቀም።

14ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። 15ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው።

ወልድ ሕይወትን ይሰጣል

16አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። 17ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። 18እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።

19ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ 20አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነ ቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። 21ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። 22አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ 23ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።

24“እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። 25እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ 27ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል።

28“በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ 29መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። 30እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው።

ጎርጎርዮስ (ሆሳዕና)

ማቴዎስ 21:1-17
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ

1ኢየሩሳሌም መቃረቢያ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደተባለችው ስፍራ እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ 2እንዲህ አላቸው “ባቅራቢያችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፤ እንደ ደረሳችሁም አንዲት አህያ ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም ወደ እኔ አምጧቸው። 3ማንም ሰው ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ፣ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት፤ ወዲያውኑ ይሰዳቸዋል።”

4ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ በማለት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።

5“ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤

‘እነሆ፤ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፣

በአህያዪቱና በግልገሏ፣

በውርንጫዪቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’ ”

6ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7አህያዪቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሶቻቸውን በላያቸው ላይ አኖሩ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው። 8ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን፣ በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ጣል ጣል አደረጉ። 9ቀድሞት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው ይከተለው የነበረው ሕዝብም እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፣

“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤”

“በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤”

“ሆሣዕና በአርያም!”

10ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች።

11ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ።

ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲነግዱ ያገኛቸውን አስወጣቸው

12ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን አባረራቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣ 13“ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን፣ ‘የዘራፊዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው።

14በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። 15ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሣዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ።

16እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ” አሉት።

ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?”

“ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣

ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ”

17ትቶአቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው አደረ።

ማርቆስ 11:1-12
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ

1ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፤ 2“በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፣ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈታችሁ አምጡት፤ 3ማንም፣ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤ በቶሎም መልሶ ይልከዋል’ ብላችሁ ንገሩት።”

4እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ እመንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙት፤ ፈቱትም። 5በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፣ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። 6ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው። 7ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሳቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት። 8ብዙ ሰዎች ልበሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። 9ከፊቱ የቀደሙትና ከኋላው የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ፤ እንዲህ ይሉ ነበር፤

“ሆሣዕና!

በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!

10የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት!

ሆሣዕና በአርያም!”።

11ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለመሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።

ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጸዳ

12በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ።

ሉቃስ 19:28-48
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ

28ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሞአቸው ይሄድ ነበር። 29ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ 30“በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። 31ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።”

32የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። 33ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው።

34እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ።

35ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። 36ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሳቸውን ያነጥፉ ነበር።

37በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል ወደ ሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤

38“በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!”

“በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!”

39በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት።

40እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው።

41ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ 42እንዲህም አለ፤ “ሰላምሽ የሚሆነውን ምነው አንቺ ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሮአል፤ 43ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከበው አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣልና፤ 44አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላ ወቅሽምና።”

ኢየሱስ በቤተ መቅደስ

45ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ ሻጮችን ከዚያ አስወጣ፤ 46ደግሞም “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው።

47በየቀኑም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ 48ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተቈራኝተው ትምህርቱን ይከታተሉ ስለ ነበር፣ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው።

ዮሐንስ 12:12-19
ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ

12በማግሥቱም ለበዓሉ የመጣው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ፤ 13የዘንባባም ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤

“ሆሣዕና!”

“በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው!”

“የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው!”

14ኢየሱስም የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤

15“የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አትፍሪ፤

እነሆ፤ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል

ተቀምጦ ይመጣል።”

16ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ስለ እርሱ የተጻፉትንና ለእርሱም የተደረጉትን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ በኋላ ነበር።

17አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ባስነሣበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መነሣቱን ይመሰክሩ ነበር። 18ብዙ ሰዎችም ይህን ታምራዊ ምልክት ማድረጉን ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። 19ስለዚህም ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፣ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? አያችሁ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።

Previous
Previous

April 19 2025

Next
Next

April 6 2025