April 2 2023
የመጀመሪያ ምንባብ
ሮሜ 7:1-18
የጋብቻ ምሳሌ
1ወንድሞች ሆይ፤ ሕግን ለሚያውቁ ሰዎች እናገራለሁ፤ ሕግ በአንድ ሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው፣ ሰውየው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን አታውቁምን? 2አንዲት ያገባች ሴት ከባሏ ጋር በሕግ የታሰረች የምትሆነው እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ነው፤ ባሏ ቢሞት ግን ከጋብቻ ሕግ ነጻ ትሆናለች። 3ነገር ግን ባሏ በሕይወት እያለ ሌላ ሰው ብታገባ አመንዝራ ትባላለች፤ ባሏ ቢሞት ግን ሌላ ሰው ብታገባም እንኳ፣ ከዚያ ሕግ ነጻ ትሆናለች፤ አመንዝራ አትባልም።
4ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተም በክርስቶስ ኢየሱስ ሥጋ ለሕግ ሞታችኋል፤ ይህም ከሙታን ለተነሣው ለእርሱ፣ ለሌላው ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ ነው። 5ኀጢአተኛ በሆነ ተፈጥሮ ቊጥጥር ሥር ሳለን፣ ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሕግ የተቀሰቀሰው የኀጢአት መሻት በሥጋችን ላይ ይሠራ ነበር። 6አሁን ግን ቀድሞ ጠፍሮ አስሮን ለነበረው ሞተን፣ ከሕግ ነጻ ወጥተናል፤ ይህም አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ አዲስ በሆነው በመንፈስ መንገድ እንድናገለግል ነው።
ከኀጢአት ጋር መታገል
7እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ በራሱ ኀጢአት ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ፣ ኀጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ፣ ምኞት ምን እንደሆነ በርግጥ አላውቅም ነበር። 8ኀጢአት ግን ትእዛዙ ባስገኘው ዕድል ተጠቅሞ በእኔ ውስጥ ማንኛውንም ዐይነት አጒል ምኞት አስነሣ፤ ኀጢአት ያለ ሕግ ምዉት ነውና። 9ሕጉ ሳይኖር ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ ከመጣ በኋላ ግን፣ ኀጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትሁ። 10ለሕይወት እንዲሆን የታሰበው ያ ትእዛዝም ሞትን እንዳመጣ ተገነዘብሁ፤ 11ኀጢአት በትእዛዝ በኩል የተገኘውን ዕድል በመጠቀም አታለለኝ፤ በትእዛዝም ገደለኝ። 12ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና መልካም ነው።
13ታዲያ በጎ የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? ከቶ አይደለም፤ ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ፤ ይኸውም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት ይሆን ዘንድ ነው።
14ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ። 15የማደርገውን አላውቅም፤ ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁና። 16ማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ፣ ሕጉ በጎ እንደሆነ እመሰክራለሁ፤ 17እንዲህ ከሆነ፣ ይህን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው። 18በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም።
ሁለተኛ ምንባብ
1 ዮሐንስ 4:18-21
18በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
19እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 20ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና። 21እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።
ወንጌል
ዮሐንስ 3:1-11
ኢየሱስ ኒቆዲሞስን አስተማረ
1ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ 2በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንህ እናውቃለን” አለው።
3ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው።
4ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው።
5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ 6ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። 7‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ 8ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።”
9ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።
10ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? 11እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም።