Ethiopian Catholic Secretariat

Covid and Mental Health-1.png

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ወቅታዊ በኮቪድ 19 ሁኔታን መሰረት በማድረግ የምክር አገልግሎት ክፍል አቋቁሞ የተለያዩ ወገኖችን በማገልገል ላይ ይገኛል። በኮቪድ 19 የተያዛችሁ እና የምትሰቃዩ፣ ቤተሰቦቻችሁ በዚህ በሽታ ተይዘው የሚሰቃዩባችሁ፣ ለበሽታው የመጋለጥ እድላችሁ የሰፋ ሰዎች (ለምሳሌ፡- የህክምና ባለሞያዎች) ሞያዊ እገዛ የምትፈልጉ ከዚህ በታች ባሉት ስልኮች ባለሙያዎችን ማግኘት ትችላላችሁ። 0905051987(ዘወትር ሐሙስ) እና 0905051906 (ዘወትር ቅዳሜ) ለማንኛውም መረጃ 0905051962 ይደውሉ በክፍሉ የተዘጋጁ ሳምንታዊ ጽሁፎችን በገጻችን ይከታተሉ። ለዛሬ የተዘጋጀውን ጽሁፍ እነሆ!

ፍርሃት እና ጭንቀት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ
በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የብዙዎችን ህይወት ስጋት ውስጥ በጣለ ጊዜ ፍርሃትና ጭንቀት በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ የደውል ድምፁን ያሰማል፡፡ በዚህ ወረርሽኝ ጊዜ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ የሚከተው በሽታው ብቻ ሳይሆን ይዞት የመጣው ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበረሰባዊ ቀውስ ነው፡፡

ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ትምህርት ቤትና የወደፊት እጣ ፋንታ ያስባሉ፡፡ ሰራተኞች ምን ያህል ጊዜ በስራ ገበታቸው ላይ መቆየት እንደሚችሉ ስለማያውቁ ይሰጋሉ፡፡ የእለት ጉርስን ማግኘት ከባድ የሆነባቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ብዙዎች ብታመምስ፣ ቤተሰቦቼ ቢታመሙስ፣ የምወዳቸው ሰዎች ህይወት እና የእኔም ህይወት በዚህ በሽታ ቢቀጠፍስ ብለው ይሰጋሉ፡፡ በበሽታው ተጠቅተው በየሀኪም ቤቱ እና በማቆያ ስፍራዎችም የሚገኙ አሉ፡፡

አይደለም በኮቪድ 19 ታሞ መሞት ቀርቶ በሌላ በሽታ ታሞ መሞት የሚያስፈራበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ በበሽታው መያዝ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምክንያት ከማህበረሰቡ መገለል በራሱ ትልቅ ጭንቀት እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር የያንዳንዱን ሰው የፍርሃት መጠን ይጨምራል፡፡

ብዙ ጊዜ ፍርሃት በንዴት ሊሸፈን ይችላል፡፡ በተለይ በዚህ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ ብዙ ሰዎች ፍርሃትን ሳይሆን ንዴትን በራሳቸው እና በሌሎች ላይ ሊመለከቱ ይችላሉ፡ ለምሳሌ በትዳር አጋሮቻቸው ላይ ወይም በልጆቻቸው ላይ ወይም በህክምና ባለሞያዎች ላይ ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ንዴት አንድን ነገር መቆጣጠር ካለመቻል የሚመነጭ አቅም አልባነት እና የመሸነፍ ስሜት ሲሆን ወደ ንዴት በቀላሉ ይቀየራል፡፡ ፍርሃት እና ጭንቀት በሶስት መንገዶች ይገለጣሉ

1. በአእምሮ (Cognitively) ፡- የማስተዋል ፣ የማሰብ፣ የማስታወስ አቅምን በመገደብ
2. በባህሪ (behaviourally) ፡- ብስጭት፣ እራስን ከሌሎች ማራቅ፣ በራስ መተማመን መቀነስ፣ ቁጡ መሆን ወይም ግዴለሽ መሆን
3. አካላዊ ለውጥ (physiological change) ፡- እንቅልፍ ማጣት፣ የአመጋገብ ችግር፣ (የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም ከመጠን በላይ መመገብ) የልብ ምት መጨመር፤ የደም ዝውውር መዛባት፤ ደም ግፊት፣ የመተንፈስ ችግር ወ.ዘ.ተ. ፍርሃት እና ጭንቀት የሚመጋገቡ ስሜቶች ሲሆኑ ሁለቱም ለአእምሮአችን ‹‹በፊት ለፊትህ አደጋ አለና ተጠንቀቅ›› የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ፍርሃት ከሚታይና ከሚጨበጥ ነገር ጋር የተያያዘ ሲሆን ጭንቀት ግን ልንይዘው ወይም ልንጨብጠው ከማንችለው እውነታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚያስጨንቀን ነገር ይህ ነው ብለን ስም መስጠት እንኴን ያዳግተናል፡፡ ሰለሆነም ጭንቀት እንደ ፍርሃት በሚጨበጥና በሚታይ ነገር ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን ‹‹ሊሆን ይችላል›› ብለን ከምናስበው ነገር ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ከፍርሃታችን ጋር በሰላም መኖር ይቻል ይሆን?
ፍርሃት ተፈጥሮአዊ ስሜት መሆኑን ማመን በመጀመሪያ ደረጃ ከፍርሃት ጋር በሰላም መኖር የምንችለው ፍርሃት ተፈጥሮአዊ ስሜት መሆኑን ስንቀበል ነው፡፡ ፍርሃት በውስጣችን ያለና የሚኖር ‹‹አደጋ አለና ተጠንቀቁ›› የሚል ውስጣዊ የሰው ልጆች የትራፊክ መብራት ነው፡፡

ፍርሃት አደጋ የሚሆነው እኛነታችንን ሲገዛ እና እስረኛ ሲያደርገን ወደ ጭንቀት ተለውጦ አእምሮአችንን ሲያውክ ነው፡፡ የፍርሃታችንን ምክንያት ማወቅ ምን እንደሚያስፈራን ማወቅና ፍርሃት ባለን ጊዜ ምን አይነት ባህሪ እንደምናሳይ ማወቅ ጎጂ ባህሪዎቻችንን ለማሻሻል ይረዳናል፡፡

ለምሳሌ ፡- በፈተና የመውደቅ ፍርሃት በደምብ እንድናጠና ሊያደርገን ይችላል፡፡ በኮቪድ 19 መያዝ የሚያስፈራን ከሆነ ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡

አንዳንድ ሰዎች ፍርሃት በሚይዛቸው ጊዜ ፍርሃታቸውን ለማሸነፍ ወደ ተለያዩ ሱሶች ውስጥ ይገባሉ፡፡ ለምሳሌ መጠጥ፣ጫት፣ ዕጽ፣ ወ.ዘ.ተ. ሱስ ፍርሃትን በጊዚያዊነት ሊቀርፈው ይችል ይሆናል ነገር ግን የፍርሃታችንን ምክንያቶች እንዳንጋፈጣቸው ስለማያደርገን መፍትሄ ከመሆን ይልቅ ጎጂነቱ ይበዛል፡፡ ፍርሃታችንን ላለመጋፈጥ በምናደርገው ሽሽት ሱሰኞች ሆነን እንቀራለን፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴ እና መዝናናት ፍርሃት እና ጭንቀት በአካላችን እና በአእምሮአችን ላይ ተጽዕኖ አላቸው፡፡ አንድ ሰው ፍርሃት ወይም ጭንቀት ውስጥ ሲሆን አካሉና አእምሮው ሌላ ጊዜ ከሚሰራው በእጥፍ ይሰራል፡፡ ይህ ደግሞ አካላን ላልተገባ ድካም እና ህመም ይዳርገዋል፡፡ እራስ ምታት፣ የጨጓራ ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ወይም መጨመር፣ ያልተፈለገ ውፍረት፣ (ይህን ተከትሎ የሚመጣ ብስጭትና በራስ የመተማመን ችሎታ መቀነስ) የሰውነት ጡንቻዎች መወጣጠር፣ የስሜት መረበሽ፣ በቀላሉ መናደድ፣ ቁጣ እና ሆደ ባሻነት፡፡ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ የሰውነት ጡንቻዎች እንዲፍታቱ ከማድረጉም ባሻገር ደስታን የሚያመነጨው ‹‹ዶፓሚን›› የሚባለው ንጥረ ነገር በአእምሮአችን እንዲመነጭ ይረዳል ይህ ንጥረ ነገር ለአእምሮ ደስታን እና ሰላም መነቃቃትን ያመጣል፡፡ የሰውነት እንቅስቃሴ የደም ዝውውር ጥሩ እንዲሆን እና ሰውነት ኦክሲጅን እንዲያገኝ ስለሚረዳ ጭንቀትን ያስወግዳል፡፡

ፍርሃትን መጋፈጥ / እራስን ማወቅ
ፍርሃትን መጋፈጥ፡፡ ሁል ጊዜ የሚያስፈሩህን ነገሮች የምንሸሻቸው ከሆነ መቼም ከፍርሃት መውጣት አንችልም፡፡ ፍርሃትን መጋፈጥ በምንፈራው ነገር ላይ ስልጣን እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ የሚያስፈሩን ነገሮችን መጋፈጥ ፍርሃት ከሚያመጣው ጭንቀት ያድነናል፡፡

እራስን ማወቅ የሚያስጨንቁንን ነገሮች ከማወቅ ጋር ይያያዛል፡፡ ከፍርሃታችንን ‹‹በስተጀርባ ምን አይነት ሀሳቦች በህሊናችንን ውስጥ ይመላለሳሉ?›› ብሎ መጠየቅ ፍርሃት የሚያመጡብንን ሀሳቦች ለመቆጣጠር እና ለመቀየር ይረዳል፡፡ እምነት የሰው ልጅ ማንነት ስነልቦናዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ነው፡፡ ስለሆነም እምነት በየቀኑ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች መቋቋም ያስችለናል፡፡ ጸሎት እና ክርስቲያናዊ ህብረት ፍርሃትን ለመግራት የሚጠቅሙ ሁለት የማይነጣጠሉ ምሶሶዎች ናቸው፡፡

ጸሎት ችግሮቻችንን ለፈጣሪ የምናዋይበት ትልቁ መንገድ ነው ማንኛውም ችግር ከፈጣሪ በላይ አይደለምና ከእርሱ ጋር መሆን ብርታትን ያጎናፅፈናል፡፡ ለዚህም ነው መዝሙረኛው ዳዊት “ለሞት በሚያስፈራ ጥቅጥቅ ጨለማ ባለበት ሸለቆ ውስጥ ባልፍ እንኴን ክፉ ነገር ይደርስብኛል ብዬ አልፈራም የጠባቂነትህ በትርና ምርኩዝ ያጽናኑኛል” የሚለው (መዝ 23:4) ከሞት የበለጠ አስፈሪ ነገር የለም፡፡

ስለ ኮቪድ 19 ስናስብ ፍርሃት የሚያመጣብን በሽታው ሳይሆን መድሃኒት ስለሌለው በበሽታው የመሞታችን እድል የሰፋ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሞትን ድል የነሳው አምላካችን ከእኛ ጋር ነውና ከፍርሃት ይልቅ መጠንቀቅን መርህ አድርገን እንያዘው፡፡

አንድ ለአንድ የሆነ የምክር አገልግሎት ማግኘት
ማንኛውም ሰው በጭንቀት እና በፍርሃት ውስጥ በሚዋጥበት ጊዜ የሚያዳምጠውና ሞያዊ እገዛ የሚያደርግለት ሰው ያስፈልገዋል ስለሆነም በተቻለ መጠን በፍርሃት እና በጭንቀት ውስጥ ስንሆን የምክር አገልግሎት መሻት ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ፍርሃት እና ጭንቀትን እንዴት መጋፈጥ እንደምንችል በጥቂቱ ብርሃን እንደሚሆኑ እርግጠኞች ነን፡፡ ፍርሃታችሁን አዳምጡ ለመግራትም ሞክሩ ፍርሃታችሁ እናንተን እንዳይቆጣጠራችሁ በጤናማ መንገድ ፍርሃታችሁን ተቆጣጠሩት፡፡

እግዚአብሔር በምህረቱ አለማችንን እና ሀገራችንን ከዚህ ወረርሽኝ ይታደግ በኮቪድ 19 የተያዛችሁ እና የምትሰቃዩ፣ ቤተሰቦቻችሁ በዚህ በሽታ ተይዘው የሚሰቃዩባችሁ፣ ለበሽታው የመጋለጥ እድላችሁ የሰፋ ሰዎች (ለምሳሌ፡- የህክምና ባለሞያዎች) ሞያዊ እገዛ የምትፈልጉ ከዚህ በታች ባሉት ስልኮች ታገኙናላችሁ 0905051987(ዘወትር ሐሙስ) እና 0905051906 (ዘወትር ቅዳሜ) ለማንኛውም መረጃ 0905051962 ይደውሉ

በምክር አገልግሎት ቡድን የተዘጋጀ ነሐሴ 16/ 2020